1. የደብረ እንቁ መተዳደሪያ ደንብ
ደብረ ዕንቊ ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጣትንና በቃለ ዓዋዲው አንቀጽ ፮ ንዑስ አንቀጽ ፩ የሰፈረውን የእግዚአብሔርን ወንጌለ መንግስት የመስበክና ትምህርቱንም የማስፋፋት ኃላፊነቷን በተሻለ ብቃት ለመወጣት የሚያስችል ወቅታዊ አመራርና አደረጃጀት የሚያስፈልጋት መሆኑ ስለታመነበትና፤ እንዲሁም ቤተ ክርስቲያኒቱ ቃለ ዓዋዲውን ከምትገኝበትን ሃገር ሕግ ጋር አስማምታ በስራ ለመተርጎም ያመቻት ዘንድ፤ ይህ የመተዳደሪያ ደንብ በቤተክርስቲየኗ አባላት ሙሉ ስምምነት ተዘጋጅቷል።
2. ገንዘብ የማሰበሰብ ሥራን በሚመለከት የወጣ ደንብ
በቤተክርስቲያን ዙሪያ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ገንዘብ የማሰበሰብ ሥራን በሚመለከት የወጣ ደንብ፡፡ በቤተክርስቲያን ዙሪያ ካሉ ምእመናንና ለጋሾች ገንዘብ በማሰባሰብ ለበጎ አድራጎትና ለቤተክርስቲያ ልማት ሥራዎች ማዋል በእጅጉ የተለመደ ተግባር መሆኑ ይታወቃል፡፡ በገዳማችንም ይሄው አሰራር የተለመደና ለረጅም ጊዜ ስንጠቀምበት የቆየን ሲሆን በዚህም ብዙ ገንቢ የልማትና የበጎ አድራጎት ስራዎች ተሰርተዋል፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ አጋጣሚዎች ይህንን በጎ ልማድ ገንቢ ባልሆነና ግልጽኀት በጎደለው መልኩ የመጠቀም አዝማሚያዎች እየታዩ መጥተዋል፡፡ ይህም ምእመኑን እንዲሁም የሰበካ አስተዳደር ጉባዔውን አላስፈላጊ ወደ ሆነ ውዝግብ ያስገባበት ሁኔታ መፈጠሩ ይታወሳል፡፡ ይህንን ውዝግብ ለመፍታት በሽምግልና የተቀመጡ ወንድሞች ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አንድ ወጥ የሆነ ደንብ ማዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን እንደ አንድ የመፍትሔ አቅጣጫ አድርገው አስቀምጠዋል፡፡
3. በደብረ እንቁ ቅድስት ማርያም ወቅዱስ ሩፋኤል ገዳም የጽዋዕ ማኅበራት አደረጃጀት የውስጥ ደንብ
ጽዋዕ፡- ማለት በቁሙ ኩባያ፣ዋንጫ፣የመጠጥ መሣሪያ የሚል ትርጉም አለው፡፡ በሌላም በኩል በጽዋ ተቀድቶ የሚሰጥም መጠጥ ጽዋዕ ይባላል፡፡ ማኅበር ማለት ደግሞ ”ኀብረ” አንድ ሆነ ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ነው፡፡ ነገር ግን ጽዋዕ የሚለው የግእዝ ግስ ምሥጢራዊ ይዘቱ ሲፈታ ”ጸውኣ” ወይም ጠራ የሚል ፍቺ አለው፡፡ ይህም ማለት የሥላሴን ስም፣ የቅድስት ድንግል ማርያምን ስም፣ የቅዱሳን መላእክትን ስም፣ የጻድቃን ሰማእታትን ስም በመጥራት በስማቸው የሚቆረስ ጠዲቅ የሚቀመስ ውሃ አዘጋጀ ማለት ነው፡፡በአንድ ላይ የጽዋ ማኅበር ማለት በአንድ ጽዋ ለመጠጣት የሚሰባሰቡ የምእመናን አንድነት ማለት ነው፡፡ በጽዋ ማኅበር መሳተፍ በረከትን ያሰጣል (መዝ 3፡8፣ ምሳ10፡7) እንዲሁም በማቴ 10፡42 ላይ እንደተገለጸው ዋጋችን በእግዚአብሔር ዘንድ አይጠፋብንም፡፡ የጽዋዕ ማህበር መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ያደረገ ሥርዓት እንደመሆኑ የራሱ የሆኑ ዓላማዎች አሉት::



